ባህር ዳር _መጋቢት 14/2018 (አኢቴ)፦ በአብክመ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ እና በአለም የስራ ድርጅት (ILO) መካከል ወጣቶችን በዲጅታል ስራ ላይ ሊያሰማራ የሚችል ለአንድ አመት የሚቆይ የፕሮጀክት ስምምነት ስራ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡ ፕሮጀክቱ ከሃያ አራት ሚሊዮን ብር በላይ በአለም የስራ ድርጅት (ILO) የተመደበለት ሲሆን ከየካቲት ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ አመት እንደሚቆይ በመስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ ተገልጿል፡፡ ፕሮጀክቱ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ከተማ የሚገኘውን የተፈናቃዮች ካምፕ መሰረት አድርጎ የዳባትና አካባቢውን ወጣቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ትኩረቱን በዲጅታል ስራ ፈጠራ ላይ እንደሚያደርግ በውይይቱ ወቅት ተብራርቷል፡፡
በማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት በአብክመ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ የቻለ ይግዛው ክልሉ የዲጅታል ስርዓትን ለማስፈንና ቴክኖሎጂን ለህብረተሰቡ ለማድረስ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው የአለም የስራ ድርጅት (ILO) ከክልሉ ጋር ለመስራት ላሳየው ቁርጠኝነት አመስግነዋል፡፡ ቢሮው ፕሮጀክቱን በውጤታማነት ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የአለም የስራ ድርጅትን (ILO) ወክለው ወ/ሪት ማርታ ጸሃይ የተገኙ ሲሆን በተጨማሪም በዙም ሚቲንግ በመታገዝ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆኑ የተለያዩ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በውይይቱ ከሁለቱም ተቋማት እንዲሁም ከሰሜን ጎንደር ዞን፣ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡

